ማሞ ለማ፤ የወገን ጦር – ወታደሮች ነበርን ለኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ፤ ማንኩሳ
ማተሚያ ቤት፤ የህትመት ዓመት የለም፤ 601 ገጽ፡፡
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ለህትመት ከበቁት የትውስታ መጻህፍት አብዛኛዎቹ በ1983
“የደርግ ጦር” ተብሎ እንዲፈርስ የተፈረደበት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት መካከለኛና ከፍተኛ
አዛዦች የተጻፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የትውስታ ህትመቶች መካከል ለታሪክ ባለሙያዎች ጉልህ
ፋይዳ ያለው ይህ መጽሀፍ አንዱ ነው፡፡
ይህ መጽህፍ በዚህ መልክ ለህትመት ከመብቃቱ በፊት ፀሀፊው የመጀመሪያውን ቅጅ አሰናድተው
በ1997 ዓ/ም ለሻማ መጻህፍት አሳታሚ የሰጡ ቢሆንም አታሚ ድርጅቱ በወቅቱ በነበረው
መንግሥት ሊደርስበት የሚችለውን ችግር በመፍራት አራት ዓመታትን አቆይቶ፤ አንዳንድ
ክፍሎችን ቆራርጦ በ2001 ዓ/ም “የወገን ጦር ትዝታዬ” በሚል ርዕስ አትሞት ነበር፡፡ ያ
የመጀመሪያ እትም 470 ገጾች ነበሩት፡፡ በ2010 ዓ/ም የተከሰተውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ
ፀሀፊው ተቆርጠው የወጡ ክፍሎችን እንደገና በማካተትና አዳዲስ ምዕራፎችን በመጨመር ይህን
601 ገጾች ያሉትን መፅሀፍ ለማሳተም በቅተዋል፡፡ ይህ የመጽሀፍ ግምገማ ያተኮረውም 601
ገጾች ባሉት እትም ላይ ነው፡፡
ፀሀፊው በ1965 ዓ/ም በ17 ዓመታቸው በውትድርና የተቀጠሩበትን አስገራሚ አጋጣሚ
ይጠቅሳሉ፡፡ በአየር ወለድ ኮማንዶነት ለመቀጠር የፈለገ ጓደኛቸውን አጅበው ሄደው እርሱ የጤና
ምርመራውን ባለማለፉ መቀጠር ባይችልም እሳቸው ግን በአንድ መኮንን ስብከት ተስበው
በመመዝገብ የጤና ምርመራውን አልፈው እንደተቀጠሩና ቤተሰባቸውን ሳይሰናበቱ ወደ ኤርትራ
እንደተጓዙ ይተርካሉ፡፡ ከዚያም በደቀመሀሪ የዘጠኝ ወር ስልጠና ወስደው በ12ኛው እግረኛ ብርጌድ
ስር ተመድበው ከረን ከቆዩ በኋላ ከባዱን ውድድር አልፈው ለ38ኛው ኮርስ ተመልምለው በሆለታ
ወታደራዊ አካዳሚ የሚሰጠውን የመኮንኖች ኮርስ አጠናቀው በም/መቶ አለቅነት ተመርቀዋል፡፡
ወደ ኤርትራም ተመልሰው በአልጌና ግንባር በሻለቃ ዘመቻ መኮንንነት ካገለገሉ በኋላ በ1976
የሻምበልነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በዚህ ማዕረጋቸው የ101ኛ ብርጌድ ዘመቻ መኮንን፤ የመክት
ዕዝ ዘመቻ መምሪያ ረዳት ኃላፊ፤ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት (ሁአሠ) የዘመቻ፤ የጥናትና
ዕቅድ መኮንን ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ1981 የሻለቅነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመጨረሻም ወደ
አዲስ አበባ ተዛውረው በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሁአሠ ቀጠና መኮንን ሆነው ሠራዊቱ
እስከተበተነበት 1983 ዓ/ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
ሻለቃ ማሞ በውትድርና ዘመናቸው የያዟቸውን ማስታዎሻዎች ሰብስበው በ1985 ወደ እንግሊዝ
ሀገር በመሰደድ ይህን በአስራ ሰባት ክፍሎች (ምዕራፎች) የተከፈለውን ግሩም መጽሀፋቸውን
ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ ሻለቃ ማሞ ከአስራ ዘጠኝ ዓመታት የውትድርና ህይዎታቸው አስራ ሰባቱን
ያሳለፉት በኤርትራ ምድር በመሆኑ በመጀመሪያዎቹ 202 ገጾች የሚተርኩት እሳቸው ስለነበሩበት
የአልጌና ግንባር ነው፡፡ ፀሀፊው በእግረኛ ተዋጊነት፤ በቃኚ ሰላይነት፤ በከባድ መትረየስ ተኳሽነት፤
በመገናኛ ሬድዮ ሠራተኛነት፤ በአዳፍኔና በመድፍ አስተኳሽነት፤ በመጨረሻም በዘመቻ መኮንንነት
በአካል የተሳተፉባቸውን ውጊያዎች በስዕላዊ አገላለጽ አልፎ አልፎም በምስል በማስደገፍ በጠራ
ቋንቋ ተርከውልናል፡፡ እግረ መንገዳቸውን የተራሮች ሰንሰለት ስለበዛበት የአልጌና ግንባር አየር
ጸባይና የተፈጥሮ ተጽዕኖ፤ እንዲሁም በአካባቢው ሰለሚገኙት የራሻይዳና የቤኒዓምር ጎሳዎች
የአርብቶ አደርነት አኗኗር ያስቃኙናል፡፡
2
ፀሀፊው በሌሎች የትውስታ መጻህፍት የማናገኛቸውን በርካታ ጉዳዮች ያጋሩናል፡፡ ከእነዚህም
መካከል አንደኛው በአልጌና ግንባር ስለሰፈረው ሠራዊት የአመጋገብ ሁኔታ ነው፡፡ “አመጋገብን
በፈጠራ ችሎታ ማዳበር” በሚል ንዑስ ርዕስ (64) ለሠራዊቱ የሚሰጠውን ደረቅ ብስኩት (ጋሌጣ)
እንዴት ወደቂጣና እንጀራ መለወጥ እንደተቻለ ይነግሩናል፡፡ በተጨማሪም በወታደሮች ዘንድ
የተከሰተውን የእንጀራ ናፍቆት ለማርካት በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ የሸክላ ሥራ ባለሙያዎች
የሸክላ አፈር አፈላልገው እንዲያመጡ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ምጣድ መስራትና እንጀራ መጋገር
እንደተቻለ ይተርካሉ፡፡ ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ በግንባሩ የተከሰተውን የጤና ችግር ሲጠቅሱ
የአንዳንድ ወታደሮች የዘር ፍሬ ሟሙቶ በመገኘቱ፤ በዚህ የተደናገጡ ወታደሮች የዘር
ፍሬዎቻቸው መኖራቸውን ለማረጋገጥ ጧትና ማታ ይዳስሱ እንደነበር ከዚህ በፊት ያልሰማነውን
ታሪክ ያጋሩናል፡፡ ይህ ችግር የተከሰተው በአልሚ ምግብ (ፕሮቲን) እጥረት መሆኑ ታውቆ የነቀዘ
ባቄላ ለሠራዊቱ መቅረብ እንደጀመረም ይነግሩናል፡፡
ሻለቃ ማሞ በአካል የተሳተፉባቸውን ውጊያዎች ታሪክ ከማጋራት ባሻገር በበላይ አዛዦች
የተፈጸሙ ወታደራዊ ስህተቶችን ነቅሰው በማውጣት ሠራዊቱ እንዴት ለውድቀት እንደበቃ
ያሳያሉ፡፡ ምን ቢደረግ ለድል ይበቃ እንደነበርም ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ በአልጌና
ግንባር ሠራዊቱን ለአምስት ዓመታት ማስፈሩ የሰው ኃይሉ እንዲመናመንና ንብረቱ እንዲወድም
ከማድረግ ውጭ ምንም አይነት ወታደራዊ ፋይዳ እንዳልነበረው በማስረዳት ፖለቲካዊ አመራሩን
ይወቅሳሉ፡፡ በዚሁ ግንባር ሠራዊቱ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ተራሮችን በእግሩ እንዲወጣና ምሽግ
እንዲቆፍር ይነገረውና በከባድ መስዋዕትነት የያዘውን ከፍታ ነጥብ ለቆ እንዲወርድ እንደሚታዘዝ
(151)፤ በመገናኛ ሬድዮ ችግር ሳቢያ በራሱ ወገን ከባድ መሳሪያ የተደበደበበት አጋጣሚ እንደነበር
(197–198) በአይናቸው ያዩትን ለምስክርነት አቅርበዋል፡፡
የትውስታ መፅሀፍ የፃፉ ሌሎች የቀድሞው ሠራዊት አዛዦች ስለቀይ ኮከብ ዘመቻ አጠቃላይ
ክንውን ቢያብራሩም ሻለቃ ማሞ ግን በነበሩበት በአልጌና ግንባር ስለተካሄደው ውጊያ በዓይናቸው
ያዩትን ታሪክ ያጋሩናል፡፡ በዘመቻው ዋዜማ የ32ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ረዳት ዘመቻ መኮንን
ሆነው መመደባቸው በአልጌና ግንባር የተደረገውን ፍልሚያ በቅርበት ለመከታተል አስችሏቸዋል፡
፡ በዚሁ ግንባር አዲስ (19ኛ) ተራራ ክፍለ ጦር መመደቡ እየተጋነነ ይወራ እንደነበር፤ ሻለቃ
ማሞ ግን ከድሮው የተለየ ነገር እንዳላስተዋሉ ጠቅሰዋል፡፡ ፀሀፈው የቀይ ኮከብ ዘመቻ የካቲት
8 ቀን፤ 1974 ዓ/ም በሁሉም ግንባሮች እንደሚጀመር የተረዳው ሻዕቢያ ዘመቻውን ለማደናቀፍ
ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ በተራራ ክ/ጦሩ ሁለት ብርጌዶች (40ኛና 41ኛ) ላይ ማጥቃት ሰንዝሮ
ከባድ ጉዳት ማድረሱን ባይነግሩንም ሰለዘመቻው ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ያካፍሉናል፡፡
ለምሳሌ ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት አንድ ብርጌድ ጦር መርተው ጭራቅ የተባለውን ተራራ
ወጥተው ምሽግ እንዲይዙ ስለመታዘዛቸው፤ እጅግ አድካሚ ከሆነ የእግር ጉዞ በኋላ ከተራራው
አናት ላይ ስለመድረሳቸው፤ 30 ኪ/ሜ ወደጠላት ወረዳ ጠልቀው በመግባት ወደግባቸው ቢጠጉም
ከናደው ዕዝ ጋር ለመገናኘት ባለመቻላቸው የወጣው ዕቅድ ከንቱ መቅረቱን በቁጭት ያወሳሉ፡፡
በዚህም ምክንያት ጠላት ከከርከበት ግንባር ኃይል በማዛወር በመልሶ ማጥቃት በውቃው ዕዝ ላይ
በመረባረቡ የወገን ጦር ከዕዝና ቁጥጥር ውጭ ሆኖ በመሸሹ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ይነግሩናል፡
፡ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ራሳቸው ባመጡት ውድቀት በውቃው ዕዝ ላይ ለደረሰው ጉዳት
ተጠያቂዎቹ 12 ወታደሮችና አንድ መኮንን ናቸው ተብለው ወንጀላቸው ሳይነገራቸውና
ሳይመሰከርባቸው በግፍ መረሸናቸውን ይተርኩልናል፡፡
ፀሀፊው በቁጭት ከሚያወሷቸው ወታደራዊ ስህተቶች አንዱ በየካቲት 1976 ዓ/ም የውቃው ዕዝ
በጠላት መጠቃት ነው፡፡ ጠላት ከፊትና ከኋላ በዕዙ ማዘዣ ጣቢያና የድርጅት ማከማቻ ላይ ከባድ
ጥቃት ቢሰነዝርም ሠራዊቱ ጥቃቱን መከላከልና መመለስ ችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠላት ስህተቱን
3
አርሞ ሌላ ጥቃት ሊሰነዝር እየተዘጋጀ እንደነበር ተጨባጭ መረጃ ለውቃው ዕዝ ቢደርስም በቂ
ዝግጅት ባለመደረጉ የሻዕቢያ ጦር መጋቢት 10 ቀን 1976 ዓ/ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ከባድ ጥቃት
መሰንዘሩን ይነግሩናል (72)፡፡ ሠራዊቱ ለሦስት ቀናት ራሱን ሲከላከል ቢቆይም ረዳት ጦር
አለመላኩንና የአየር ድጋፍ አለመደረጉን በማስታወስ የበላይ አመራሩን ይወቅሳሉ፡፡ በስድስት
ሰዓት ጉዞ መድረስ ይችል የነበረው 29ኛው ዘርዓይ ደረስ ሜካናይዝድ ብርጌድ ቀምጨዋ ላይ
ያለምንም ሥራ ተቀምጦ እንደነበርም በቁጭት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ውድቀት የተነሳ ሽንፈት አናይም
ብለው የራሳቸውን ህይዎት የቀጠፉ ወታደሮችና አዛዦች እንደነበሩም በምሬት ያስታውሱናል፡፡
ከእነዚህ መካከል የብርጌድ አዛዥ የነበረው ሻለቃ መርሳ ራሱ ላይ የእጅ ቦምብ አፈንድቶ እንደተሰዋ
ይገልጻሉ (78)፡፡ በመጽሀፉ ውስጥ ከተካተቱ አስገራሚ ክስተቶች መካከል በመሳህሊት ግንባር
በ1969 ውጊያ ላይ ተሰውቷል ተብሎ ከተገነዘ በኋላ በተአምር የተረፈው መትረየስ ተኳሽ ታሪክ
ይገኝበታል (212–214)፡፡
በጦር ሜዳ የሚሰው የሠራዊቱ አባላትን በሚመለከት ፀሀፊው ሌላም የሚጨምሩልን መረጃ አለ፡
፡ አንድ ሰው በወታደርነት ሲቀጠር እሳት ከማያቀልጠው ብረት የተሰራ የአንገት ሀብል ይሰጠዋል፡
፡ ከብረቱ ላይ የወታደሩ መለያ ቁጥር ይታተምበታል፡፡ መለያ ቁጥሩ ስለወታደሩ ዝርዝር መረጃ
ይሰጣል፡፡ አንድ ወታደር ውጊያ ላይ ቢሰዋና አስከሬኑን ማንሳት ባይቻል መለያ ቁጥሩ በጥርሶቹ
መካከል ተስተካክሎ ከተቀመጠ በኋላ በወደቀበት ቦታ ይቀበራል፡፡ ከዓመታት በኋላ አፅሙን
አውጥቶ በሌላ ቦታ ማሳረፍ ቢያስፈልግ በጥርሱ መካከል የተቀመጠው ብረት ማንነቱን ለመለየት
እንደሚያስችል የምንረዳው ከዚሁ መጽሀፍ ብቻ ነው፡፡
ሌላው ጉልህ የመጽሀፉ ፋይዳ እስካሁን ያልሰማናቸውን አዳዲስ መረጃዎች መፈንጠቁ ነው፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ በአስመራ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የወታደሮችና መኮንኖች ሚስቶች በማህበር
ተደራጅተው የሰሩት አኩሪ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሀገር ወዳድ ሴቶች እኛም የራሳችን አበርክቶ
ማድረግ አለብን በማለት በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ሰጭነት በመሰልጠን ቁስለኞችን በማከም፤
በማስታመም፤ በመንከባከብ፤ ልብሳቸውን በማጠብ፤ ምግባቸውን በማዘጋጀትና በግንባር ድራማ
በማሳየት ታላቅ ሥራ አከናውነዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ፀሀፊው በ1981 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
ዘመቻ መምሪያ ጽ/ቤት በመመደባቸውና በመጨረሻም በታላቁ ቤተመንግስት በሚገኘው አብዮታዊ
ዘመቻ መምሪያ ቢሮ ውስጥ በመስራታቸው ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ/ም የተሞከረውን መፈንቅለ
መንግሥት በቅርብ የመከታተል ዕድል ስለሰጣቸው አዳዲስ መረጃዎችን ለማካፈል አስችሏቸዋል፡
፡ ለአብነት ያህልም ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው አንድ ቀን ቀደም ብሎ (ግንቦት 7 ቀን
1981) የሁአሠ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ሜ/ጄ ወርቁ ቸርነት ከአስመራ ወደከረን ተጉዘው
ለግንባሩ አዛዥ (ሜ/ጄ ሁሴን አህመድ) ሳያሳውቁ ከፖለቲካ ክፍል ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ አድርገው
እንደነበር ተጨባጭና አስተማማኝ መረጃ ማግኘታቸውን አስፍረዋል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት
ሙከራው እንደከሸፈም በሜ/ጄ ስዩም መኮንንና በሜ/ጄ መርዕድ ንጉሤ መካከል ስለተደረገው
የስልክ ድርድር ራሳቸው ሜ/ጄ ስዩም እንዳጫዎቷቸው ይነግሩናል፡፡ በተጨማሪም የሁአሠ ዘመቻ
መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ብ/ጄ ታደሰ ተሰማ ከህወሀት መሪዎች ጋር ያደረጉት የሬድዮ ግንኙነት
ተጠልፎ ሠራዊቱ እንዲሰማው መደረጉ አየር ወለዱ ጦር በአዛዦቹ ላይ እንዲነሳሳ ማድረጉን፤
ከአስመራ የተነሳ አንቶኖቭ አውሮፕላን በህወሀት ቁጥጥር ስር ወደነበረችው መቀሌ ከተማ ደርሶ
መመለሱ መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሾቹ ከጠላት ዶላር ተቀብለዋል የሚል ሀሜት እንዲዛመት
ምክንያት መሆኑንና ተሰነይ ደርሶ የተመለሰው አውሮፕላንም ተመሳሳይ ትርጉም ተሰጥቶት
እንደነበር ሰፊ ሽፋን (50 ገጾች) በሰጡት በዚሁ ክፍል ያስረዳሉ፡፡
4
ፀሀፊው የሚያካፍሉን ሌላው አዲስ መረጃ በ1983 ዓ/ም የአማጽያኑ ጦር አዲስ አበባን ለመያዝ
በተቃረበበት ወቅት ዋና ከተማዋ ከመንግስት እጅ ከወጣች በሚል እሳቤ በተለዋጭ ማዘዣ ጣቢያ
መከላከል ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ በሜ/ጄ ዘለቀ በየነና በብ/ጄ ጌታቸው ሽበሺ ተጠንቶ
ለፕሬዚዳንት መንግስቱ ቀርቦ እንደነበር የሚያስረዳው ነው፡፡
ለታሪክ ተመራማሪዎች ታላቅ ግብአት የሚሆነው ይህ መጽሀፍ የተሟላ ይሆን ዘንድ ጥቃቅን
የቃላት ግድፈቶቹንና የመረጃ መዛባት ያስከተሉ ስህተቶችን መጠቆሙ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ
የወገን ሠራዊት በወራሪው የሶማሊያ ጦር ላይ በጅጅጋ ግንባር ታላቅ ድል የተቀዳጀው የካቲት
26 ቀን፤ 1970 ዓ/ም እንጂ ጥር 26 ቀን አይደለም፡፡ በተጨማሪም በወረራው መጀመሪያ የጠላት
ጦር በደቡብ ግንባር ዘልቆ የገባው 500 ኪ/ሜ ሳይሆን 250 ኪ/ሜ ገደማ ነበር፡፡ በወታደሮች
መካከል የሚኖረው የመተማመንና የአብሮነት ጓዳዊ ስሜት (esprit de corps) ወታደራዊ ሞራል
ተብሎ ተዛብቶ ተተርጉሟል፡፡
በመጨረሻም ታሪኩን እንዲደግፉ የተካተቱት 28 ፎቶዎች በቂ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ
አንዳንዶቹ መጠናቸው በጣም ያነሱ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ግድፈቶች በሚቀጥለው
እትም መታረማቸው የመጽሀፉን ፋይዳ ይበልጥ ያጎላዋል፡፡
ፋንታሁን አየለ፤
ተባባሪ ፕሮፌሰር
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ